የዛፍ እና የጦጣ ፖለቲካ፤

አብይም የዛፍ ፖለቲካውን፤ ጃዋርም የጦጣ ፖለቲካውን እንደያዙ አቻችሎ ሊያኖር የሚችል አገር መፍጠር ይቻል ይሆን? ብዮ አሰብኩና ለጊዜው የመጣልኝ መልስ ሁሉም ከሕግ በታች ሲሆኑ እዳው ገብስ ይሆናል ብዮ ተውኩት። ዛፍ እና ጦጣን ያቀናጀው ተፈጥሯዊ መተሳሰር በኛ ፖለቲካም ውስጥ ቁልጭ ብሎ ይታያል። አብይ ያለጃዋር፤ ጃዋር ያለ አብይ አይነት ነገር። በአደባባይም ሲነገር እንደምሰማው እኛ ባንታገል ኖሮ እነ አብይ ሥልጣን አይዙም ነበር የሚል እና እነ አብይ ባይሆኑ ኖሩ ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ጃዋር ዛሬ ከጦጣ ጋር የሚጫወተው ቅሊንጦ ይሆን ነበር የሚል።

ጃዋር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የጦጣን ገጸ ባህሪ ተላብሶ ታዩበታላችሁ። በብዙ ንግግሩ እና አስተሳሰቡም ውስጥ ይህን ባህሪውን ታዩታላችሁ። ከጠቅላዩ አንስቶ ያሻውን ያዋርዳል፣ አንዳንዴም ሊያስፍራራ እና ሊያሸማቅቅም ይሞክራል፣ የሚፈልገውን ሰው ይክባል፣ የካበውን ሰው ሲፈልግ ከአፈር ይቀላቅለዋል፣ አንዳንዴም በሕዝብ ላይ ይሳለቃል፣ አንዳንዴም ልክ እንደሚያጫውታት ጦጣ ከዛፍ ዛፍ እንደልቧ እና በፍጥነት እንደምትንጠላጠልው ሁሉ እሱም ከአንድ አስተሳሰብ ወደ ሌላኛው ጫፍ፣ ከአንድ ሥራ ወደ ሌላ ለመንጠላጠል ጊዜ እና ቦታም አይገድቡትም። የለውጥ አቀንቃኝ፣ አክቲቪስት፣ የፖለቲካ ተንታኝ፣ የሚዲያ አስተዳዳሪ፣ የአገር ሽማግሌ፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ፣ ሲነጋ ሌላ ሰው ሆኖ ልታገኙት ትችላላችው። በዛ ብቻም ሳይወሰን ለብዙ ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቅ ምክንያት የሆነም ፖለቲከኛ ነው። በሕግ የሚያስጠይቁትን በርካታ ነገሮች በማን አለብኝነት የሚፈጽም ግን ጠያቂ የሌለው ሰው።

ጠቅላዩ ደግሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ልክ እንደ ሚተክሉት ዛፍ የሚያዩት ይመስለኛል። ገና ችግኝ፣ ከቁርጭምጭሚት ከፍ ያላለ፣ እሳቸው ውሃ አጠጥተው፣ አፈር አሳቅፈው ሊያሳድጉት ቆርጠው የተነሱ መሆኑን በብዙ ንግግሮቻቸው ውስጥ ይደመጣል። የዛፍ እድገቱ አዝጋሚ ነው። ፍሬ ለማፍራትም ሆነ ጥላ ለመሆን በርካታ አመታትን ይፈልጋል። የኢትዮጵያንም ፖለቲካ ከችግኝነት ወደ ዛፍ ለማድረስ ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ። በፖለቲካው ጉዟቸው እና በተለይም ከለውጡ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የሚወስዷቸው እርምጃዎች አገሪቱ የገባችበትን አጣብቂኝ እና አጣዳፊ ሁኔታ ያላገናዘበ እና አዝጋሚም የሚሆኑት ለዛ ይመስለኛል። በልባቸው ውስጥ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ልክ እንደ ችግኙ የሚያዩት ይመስለኛል። በመሃል የሚነሱትን ግርግሮች፣ የፖለቲካ ትኩሳት እና ውጥረቶች ልክ ንፋስ፣ ዝናብ እና ጸሃይ እንደሚፈራረቁበት ችግኝ የሚቆጥሩትም ይመስላል። በውስጣቸው ችግኙ ይሄን ሁሉ ፈተና ተቋቁሞ ዛፍ ይሆናል የሚል ጽኑ እምነትም ያለ ይመስላል።

እንግዲህ ይህን የዛፍ እና የጦጣ ተፈጥሯዊ መስተጋብር ሁለቱ ሰዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳክቶላቸው ይተገብሩታል ወይ የሚለው ነው ትልቁ ጥያቄ። ችግኙ ዛፍ ይሆናል ወይ? ጦጣዋስ ችግኙ ዛፍ እስኪሆን ትታገሳለች ወይ? አንዳችን ዛፍ፣ ሌላችን ጦጣ ሆነን እንድንቀጥል የሚፈቅድ ፖለቲካዊ መስተጋብር መጨረሻው ምን ይሆን? 

በዚህ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን አረንጓዴ ለማልበስ በዛፍ ተከላ ላይ የጀመሩትን ትልቅ ዕራይ ያዘለ እንቅስቃሴ ከልቤ አደንቃለሁ። ጃዋርም ከጦጣዋ ጋር የመጫወት መብቱን ሙሉ በሙሉ አከብራለሁ። መልዕክቴን ከዛፍ ተከላው እና ከጦጢት ጋር በቀጥታ እንዳታያይዙት አደራ። ማተኮር የፈለኩት የሕግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ የከተተውን የሁለቱን ሰዎች ውል አልባ ቁርኝት ነው።

ያሬድ ኃ/ማርያም


Comments

Popular Posts