እራስን  በራስ  የማስተዳደር  መብትና  የኢትዮጵያ  ፌዴራሊዝም
ክፍል 1
ከአለማችን ህዝብ 40 በመቶ የሚሆነዉ የሚኖረዉ ፌዴራል የመንግስት መዋቅርን በሚከተሉ አገሮች ዉስጥ ነዉ። ይህ ማለት ግን ፌዴራሊዝም ብዙ አገሮች ዉስጥ አለ ማለት አይደለም ፥ እንዲያዉም 150 የአለም አገሮች አሃዳዊ የመንግስት መዋቅርን ነዉ የሚከተሉት። አሃዳዊ የመንግስት መዋቅር ዛሬ አዳዲሶቹ የአገራችን ጥራዝ ነጠቆች እንደሚነግሩን ፀረ ዲሞክራሲ ወይም ፀረ አንድነት አይደለም። ዲሞክራሲ  አሃዳዊ ወይም ፌዴራሊዝም ብሎ ነገር አያዉቅም። በሁለቱም ዉስጥ ያለ ምንም ችግር እራሱን መግለጽ ይችላል። ለምሳሌ ጃፓን፥ ፈረንሳይና እንግሊዝ አሃዳዊ የመንግስት መዋቅር ያለባቸዉ አገሮች ሲሆኑ አሜሪካ፥ ጀርመንንና ካናዳ ደግሞ ፌዴራል የመንግስት ስርአትን የሚከተሉ አገሮች ናችዉ። እነዚህ ስድስት አገሮች ጠንካራ አንድነት አላቸዉ፥ ሁሉም የአለማችን ሃብታም አገሮች ናቸዉ፥ ሁሉም የአለማችን የዲሞክራሲ ምልክቶች እና G 8 ቡድን አባላት ናቸዉ።
አገሮች ፌዴራሊዝምን የመረጡበት የየራሳቸዉ የሆነ ምክንያት አላቸዉ። ፌዴራሊዝም አንዳንድ አገሮች ዉስጥራስን በራስ የማስተዳደርጥያቄ መልስ ነዉ፥ አንዳንድ አገሮች ዉስጥ ትልቅ የጋራ ገበያና ጠንካራ ኢኮኖሚ የመፍጠር ፍላጎት ዉጤት ነዉ። አንዳንድ አገሮች ዉስጥ ደግሞ ፌዴራሊዝም በተለያዩ ቡድኖች መካከል ለሚነሱ ግጭቶችና አለመግባባቶች ዕልባት ለመስጠት የሚወሰን አገራዊ ዉሳኔ ዉጤት ነዉ። አንዴትም ተፈጠረ እንዴት ፌዴራሊዝም በፍጹም የማይለዩት  ሁለት ትልልቅ መታወቂያ ካርዶቹ አሉት- አንደኛዉ የጋራ አስተዳደር (Shared-rule) ሲሆን ሁለተኛዉ ራስን በራስ ማስተዳደር (Slef-rule) ናቸዉ። እነዚህ ሁለት እሴቶች በሌሉበት ቦታ ስለ ፌዴራሊዝም ማዉራት አይቻልም። አሃዳዊ የመንግስት መዋቅር ኖሯቸዉ ከዲሞክራሲ ጋር የማይተዋወቁ  አገሮች አሉ፥ ፌዴራሊዝምና ድሞክራሲ ግን  ተነጣጥለዉ መኖር አይችሉም።

Comments

Popular Posts