እራስን
በራስ
የማስተዳደር
መብትና
የኢትዮጵያ
ፌዴራሊዝም
ክፍል 5
ኢትዮጵያ ዉስጥ ሉዓላዊነት፥ ማንነትና የመሬት ባለቤትነት የተቆራኙ ነገሮች ስለሆኑ ብሄር ብሄረሰቦች ከተማን በተለይ ህብረብሄር ከተማዎችን ማስተዳደር እንደማይችሉ አዋሳ ዉስጥ በተግባር ታይቷል። አዋሳን የመሰለች የአገር ዉስጥና የአለም አቀፍ ጎብኚዎች ማግኔት የነበረች ዉብ ከተማ ዛሬ ዉበቷን ጥላቻ ጋርዶት ማግኔትነቷን ክፋትና ጭካኔ አድብዝዞት አዋሳ ህይወት የሌለባት ከተማ መስላለች። ህብረ ብሄር በሆኑ የተለያዩ የአገራችን ከተማዎች ዉስጥ በግልጽ እንደሚታየዉ ከተማዎችን የሚያስተዳድሩ ሰዎችና በከተማዎች ዉስጥ ያለዉ የፖሊስ ሀይል ከከተማዉ ነዋሪ ህዝብ ጋር አለመመሳሰላቸዉ ብቻ ሳይሆን ሆድና ጀርባ ናቸዉ። በከተማዎች ዉስጥ የሚኖረዉ ህዝብ ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የመጣ ህዝብ ነዉ። በክልል እየተሾሙ ከተማዎችን የሚያስተዳድሩ ሰዎች ግን የክልሉ ባለቤት ነኝ የሚለዉ ብሄር አባላት ናቸዉ። ለምሳሌ ከ1997 ዓም ጀምሮ
የአዋሳ ከንቲባና የከተማዋ ምክር ቤት አባላት በአዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ያልተመረጡ የሲዳማ ብሄር ተወላጆች ናቸዉ። ይህ ከዲሞክራሲ ጋር የማይተዋወቅና የከተማ ነዋሪዎችን የዜግነት መብት የገፈፈ ወገናዊ አሰራር መቆም አለበት። ኢትዮጵያ ዉስጥ በወረዳ ደረጃ ካለዉ የአስተዳደር እርከን ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ዉስጥ የሚኖረዉ ህዝብ መመራት ያለበት በክልል ደረጃ በሚሾሙ ሰዎች ሳይሆን እራሱ በመረጣቸዉ መሪዎች ብቻ መሆን አለበት።
አዲስ አበባን ጨምሮ አንዳንድ ትላልቅ ህብረብሄር ከተማዎችን “የኛ ናቸዉና” ክልላችን ዉስጥ መካተት አለባቸዉ የሚልና ህዝብን ለግጭት የሚጋብዝ ኢ-ምክንያታዊ ድምፅ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየበረከተ መጥቷል። ለምንድነዉ ብሄር ብሄረሰቦች ህብረብሄር ህዝብ የሚኖርባችዉን ከተማዎች ካላስተዳደርን የሚሉት? ለምንድነዉ በከተማዎች የሚኖረዉ ህዝብ ከሱ ጋር በማይኖሩና በማያዉቃቸዉ ተሿሚዎች የሚመራዉ? ለምንድነዉ ብሄር ብሄረሰቦች እነሱ በትግላችን አገኘን የሚሉትን እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከከተማዉ ህዝብ ላይ መቀማት የሚፈልጉት? ላለፉት አርባና ሃምሳ አመታት ጫካ ገብተን የታገልነዉ ህዝብ የራሱን ጉዳይ በራሱ የመወሰን መብቱ እንዲከበር ነዉ ብለዉ አፋቸዉን ሞልተዉ የሚነገሩን የብሄር ልህቃን ለምንድነዉ የአዲስ አበባ ፥ የመቀሌ
፡ የድሬደዋ ፥ የጂማ ፥ የሐረር ፥ የባህርዳር ፥ የደሴ ፥ የአዳማ ፥
የአዋሳ ወዘተ ህዝብ የራሱን ጉዳይ በራሱ መወሰን እንድችል የማይተዉት ወይም ዕድል የማይሰጡት? ተምቤንን፥አንደርታንና ዕሮብን የሚያስተዳድሩ አስተዳዳሪዎችን ለምንድነዉ ህወሓት ብቻ የሚሾመዉ? ለምንድነዉ የእነዚሁ አካባቢ ህዝብ የራሱን መሪዎች ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየመረጠ እራሱ ላይ መሾም እንድችል ዕድል የማይሰጠዉ? ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ቆርጫለሁ እያለ የሚነግረን የኢትዮጵያ መንግስት መቼ ነዉ
ኢትዮጵያ ዉስጥ በዞን፥ በወረዳና በየከተማዉ የሚኖረዉ ህዝብ መሪዎቹን እንዲመርጥ መንገድ የሚያመቻቸዉ? በሚቀጥለዉ ምርጫ ይህ የማይሆን ከሆነ የትኛዉ ምርጫ ነዉ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ይሆናል እየተባለ የሚነገረን? ለመሆኑ ሲጀመር መሪዎቹን መምረጥ የማይችል የዞን፥ የከተማና የወረዳ ህዝብ ስለነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማዉራትስ ይችላል?

Comments
Post a Comment
Thank You!!