እራስን  በራስ  የማስተዳደር  መብትና  የኢትዮጵያ  ፌዴራሊዝም
ክፍል 6
ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን ፌዴራል ስርአት ከዉጭ ሆኖ የሚመለከት ሰዉ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም እንደማንኛዉም አገር ፌዴራሊዝም በየአካባቢዉ ለሚኖር ህዝብ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚሰጥ ይመስለዋል። ጉዳዩ ግን ወዲህ ነዉ። የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ለህዝብ የሚሰጠዉእራስን በራስ የማስተዳደርመብት የሚጀምረዉም የሚያበቃዉም ክልል ላይ ነዉ። ከክልል በኋላ በዞን፥ በከተማና በወረዳ ደረጃ ያለዉ አሰራር በሙሉ አሃዳዊ አሰራር ነዉ። ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ በዞን፥ በከተማና በወረዳ ደረጃ የሚኖረዉን ህዝብ እላዩ ላይ ቁጭ ብለዉ አድርግ አታድርግ የሚሉት በቀዳማዊ /ሥላሤና በደርግ ዘመን እንደሚደረገዉ ከማዕከል እየተሾሙ የሚመጡ ሹሞች ናቸዉ። ይህ ደግሞ ከዋና ዋናዎቹ የፌዴራሊዝም መሰረተ ሃሳቦች ጋር የሚጻረር አሰራር ነዉ። ለምሳሌ የአዳማና የሐረር ከተማ ህዝብ፥ የሃዲያና የወላይታ ዞን ህዝብ፥ ወይም በየትኛዉም የአገራችን አካባቢ በወረዳዎች የሚኖረዉ ህዝብ ክልል እየሾመ በሚልካቸዉ ሹሞች ነዉ የሚመራዉ እንጂ ይመሩኛል ብሎ የሚተማመንባቸዉን የራሱን መሪዎች የመምረጥ ዕድል የለዉም። ይህ የሚነግረን ኢትዮጵያ ዉስጥየራስን ጉዳይ በራስ መወሰንየሚባለዉ መሰራታዊ የሰዉ ልጆች መብት በህገ መንግስት ደረጃ ይቀመጥ እንጂ ይህንን መብት በህገ መንግስቱ ዉስጥ ያስቀመጡ ሰዎችም ሆኑ ዛሬ መብቱን እየጠየቁ ያሉ ሰዎች ከራሳቸዉ የግል ጥቅምና ፍላጎት ዉጭ ለዜጎች መብትና ነጻነት ምንም ግድ እንደሌላቸዉ ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ እራሳቸዉን የፌዴራሊዝም አባት አድርገዉ የሾሙና ፌዴራል ስርአቱ መሻሻል አለበት የሚሉ ሃይሎችንአሃዳዉያንእያሉ የሚጠሩት እንዲህ አይነቶቹ ህዝብን የትም ሆንክ የት የምናስተዳድርህ እኛ ብቻ ነን የሚሉና በፌዴራሊዝም ካባ ህዝብን ጨፍልቀዉ የሚገገዙፌዝ-ራሊስቶችናቸዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ የክልልና የፌዴራል ፓርላማ ተወካዮቹን ስለመረጠ ብቻ እራሱን በራሱ ያስተዳድራል ሊባል አይቻልም። አንድ ህዝብ እራሱን በራሱ ያስተዳድራል የሚባለዉ በእያንዳንዱ የአስተዳደር እርከን ደረጃ የሚኖር ህዝብ መሪዎቹን ያለምንም ተፅዕኖ እሱ እራሱ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጥ ሲችል ብቻ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ፌዴራል ስርአት ይህንን አይፈቅድም። አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ የዲሞክራሲ መሰረት እየጣልን ነዉ የምንል ከሆነ ይህ መሰረት መጣል ያለበት ከወረዳ ጀምሮ ነዉና ወረዳዎችና ዞኖች መሪዎቻቸዉን፥ከተማዎች የምክር ቤት አባላቶቻቸዉንና ከንቲባቸዉን ክልሎች ደግሞ ፕሬዚደንቶቻቸዉን በቀጥታ በሚሰጥ ድምፅ  መምረጥ መቻል አለባቸዉ። እርግጠኛ ነኝ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ለህዝብ ታገልኩ የሚል የፖለቲካ ልህቅ የህዝብን ምርጫ የሚፈራ አይመስለኝም! ደግሞም በንጉሱና በወታደራዊዉ በደርግ ዘመን ያልወደድናቸዉን የማዕከል ተሿሚዎች ዛሬ የምንወድበት ምንም ምክንያት የለም!!!
ኢትዮጵያ ዉስጥ በዞን፥ በከተማና በወረዳ ደረጃ የሚኖረዉ ዜጋ የዜግነት መብቱ ተከብሯል ማለት የሚቻለዉ ይህ ዜጋ በሚኖርበት አካባቢ የራሱን ጉዳይ እራሱ መወሰን ሲችል ብቻ ነዉ።በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ እራሳቸዉን በአንድ ብሄር መነጽር የማይመለከቱና ከክልላቸዉ ወጥተዉ በሌሎች ክልሎች ዉስጥ የሚኖሩ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ሰብዓዊ፥ ዲሞክራሲያዊና የሲቪክ መብት ሊከበር የሚችለዉ እነዚህ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ሁሉ በመረጧቸዉ መሪዎች ሲመሩ ነዉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ከሚቀጥለዉ ምርጫ በፊት በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የራሱን ጉዳይ በራሱ መወሰን የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት። 2012 ምርጫ በተያዘለት የግዜ ሰሌዳ ካልተካሄደ አገር ይበጠበጣል እያሉ የሚያስፈራሩን የፖለቲካ ልህቃኖቻችንም የኢትዮጵያ ህዝብእራስን በራስ የማስተዳደርመብት በክልል ደረጃ ብቻ በተገደበበት አገር ዉስጥ ምርጫ ማካሄድ ማለት በፌዴራሊዝምና በዲሞክራሲ መቀለድ ወይም ሁለቱንም አለማወቅ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የዜጎች በየእርከኑ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት መከበሩ፥ ነጻና ገለልተኛ የምርጫ ሂደት መኖሩና ምርጫዉ ነጻና ፍትሃዊ መሆኑን የሚያረጋግጡ ተቋማት መኖራቸዉ መረጋገጥ አለበት።
ቸር እንሰብት

Comments

Popular Posts