እራስን  በራስ  የማስተዳደር  መብትና  የኢትዮጵያ  ፌዴራሊዝም
ክፍል 2
ኢትዮጵያ ፌዴራል የመንግስት መዋቅርን ከሚከተሉ 25 የአለማችን አገሮች ዉስጥ አንዷ ናት። ፌዴራሊዝም የተለያዩ ሉዓላዊ አገሮች አብረን እንኑር ብለዉ ተደራድረዉ የሚፈጥሩት ወይም የአንድ ሉዓላዊ አገር ልህቃን በአካባቢ እራሳችንን እናስተዳድር ብለዉ ተደራድረዉ የሚፈጥሩት ስርአት ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ፌዴራሊዝም የተፈጠረዉ ከሁለቱም መንገዶች በተለየ መንገድ ነዉ። 1980ዎቹ አጋማሽ ኢትዮጵያ ዉስጥ ህገ መንግስት የጻፈዉ፥ የፌዴራል ስርአቱን የፈጠረዉና ፌዴራል ስርአቱን ለመፍጠር የተደራደሩትን አካላትንም በራሱ አምሳል የፈጠረዉ ህወሓት ነዉ። ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች፥ ሃይማኖት፥ ቋንቋና የባህል ስብስቦች ለሚገኝባቸዉ አገሮች ሁነኛ የመንግስት መዋቅር ነዉ። ሆኖም ፌዴራሊዝም የአንድ አገር ህዝብና የተለያዩ የፖለቲካ ባለድርሻዎች ተስማምተዉ የሚፈጥሩት ስርአት ነዉ እንጂ አንድ ቡድን በሌሎች ላይ የሚጭነዉ ጭነት መሆን የለበትም። የኢትዮጵያ ፌዲራሊዝም አንደኛ - ሲመሰረት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ፌዴራሊዝም አይደለም ፥ ሁለተኛ- ዲሞክራሲ አልባ ፌዴራሊዝም ነዉ ፥ ሶስተኛ - በአካባቢም በማዕከልም የፖለቲካ ስልጣንን ጠቅልሎ የያዘና በፌዴራሊዝም የተለበደ አሃዳዊ ስርአት ነዉ። ለምሳሌ ህወሓት የበላይ በነበረበት ዘመን በተለይ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ግዜ የክልል ፕሬዚደንትና የደኢህዴን፥ የብአዴንና የኦህዴድ /መንበር ሆነዉ የሚሾሙት ሰዎች የግድ የህወሓትን እዉቅና ማግኘት ነበረባቸዉ።
 የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ኢትዮጵያ ፌዴራል የመንግስት መዋቅርን የምትከተል አገር መሆኗን በግልጽ ይናገራል፥ ሆኖም ዛሬ በተግባር እንደሚታየዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኮንፌዴሬሺን እንጂ ፌዴራሊዝም የሚባል ነገር ያለም አይመስልም። ክልሎች ከፌዴራል መንግስቱ ጋር የሚገዳደር፥ ታማኝነታቸዉ ለፍትህና ለህግ የበላይነት ሳይሆን የኛ ነዉ ለሚሉት ክልል ብቻ የሆነ የታጠቀ ልዩ ሃይልና ፖሊስ አላቸዉ። በክልሎችና በፌዴራሉ መንግስት መካከል ያለዉ ግኑኝነት የላላ ነዉ፥ አንዳንድ ክልሎች ጭራሽ ለፌዴራሉ መንግስት አይታዘዙም። የፌዴራሉ መንግስት በተለይ የመከላከያ ሰራዊታችን በክልሎች ዉስጥ እንደ ባዕድ አካል የሚታይበትና አንዳንዴም ይዉጣልን የሚባልበት ግዜ አለ። እንዲህ አይነቱ ህግ የማይገዛዉ ዕብጠት ሊፈጠር የቻለዉ ህገ መንግስቱ ሲጻፍና ፌዴራል ስርአቱ ሲዋቀር ትልቅ ትኩረት የተሰጠዉ ለብሄር ብሄረሰቦች መብት ብቻ እንጂ ይህ መብት በተግባር እንዴት እንደሚገለጽ ምንም የተባለ ነገር ባለመኖሩ ነው። ለምሳሌ ህገ መንግስቱ ብሄር ብሄረሰቦች እንዴት አብረዉ በሰላም ይኖራሉ፥ እያንዳንዱ ክልል አካባቢዉን ለማስተዳደር የሚያስችል የቆዳ ስፋት፥ በቂ ሀብትና የሰዉ ሃይል አለዉ ወይ፥ ክልሎችና የፌዴራል ስርአቱ የሚኖራቸዉ ግኑኝነት ምን መምሰል አለበት፥ አገሪቱ ዉስጥ ከፍተኛዉ ስልጣን የማነው? የፌዴራሉ መንግስት ወይስ የክልሎች፥ ኢትዮጵያ ዉስጥ የዜጎች መሰረታዊ መብት ሲጣስ ማነዉ የሚደርስላቸዉ፥ የፌዴራሉና የክልል ህገ መንግስት ሲጋጭ የትኛዉ ህገ መንግስት ነው ተፈጻሚ የሚሆነዉ ለሚሉና ለሌሎችም መሰረታዊ ጥያቄዎች ምንም ትኩረት አልሰጠም። ዛሬ አገራችንን የባህር ላይ ሞገድ እንደመታዉ መርከብ የሚያናዉጣት የእነዚሁ ትኩረት ሳይሰጣቸዉ የታለፉ ጥያቄዎች መዘዝ ነዉ።  

Comments

Popular Posts