እራስን
በራስ
የማስተዳደር
መብትና
የኢትዮጵያ
ፌዴራሊዝም
ክፍል 4
ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ የብሄር ፖለቲካ አራማጆች ብረት አንስተን የታገልነዉ የህዝብን የ”ራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን” መብት (Self-determination) ለማስከበር ነዉ
ይላሉ። እነሱ ህዝብ የሚሉት ግን ብሄር ብሄረሰብ ብለዉ የሚጠሩትን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነዉ። ከዚህ ዉጭ ያለዉ ከተለያዩ ብሄሮች የሚወለድና እራሱን ከአንድ ብሄር የማይቆጥር በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዜጋና ከራሱ ክልል ወጥቶ ሌላ ክልል ዉስጥ የሚኖር ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን ቀርቶ የኔ ነዉ የሚለዉን ተወካዩን መምረጥም አይችልም። ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዉስጥ ቁጥሩ እጅግ በጣም ብዙ የሆነ እራሱን አማራ ብሎ የሚጠራ ህዝብ በገጠርም በከተማም ይኖራል፥ ሆኖም ይህ ህዝብ የፌዴራል መዋቅሩና የምርጫ ስርአቱ በጣምራ በፈጠሩበት ችግር የተነሳ ቁጥሩን በሚመጥን መልክ ጨፌ ኦሮሚያ ዉስጥም ሆነ በአገራዊዉ ፓርላማ ዉስጥ ጥቅሜንና ፍላጎቴን ይወክሉልኛል የሚላቸዉን የራሱን ተወካዮች መምረጥ አይችልም።
የ”ራስን ጉዳይ በራስ መወሰን” የሚለዉ መርህ አንድ ዉሳኔ የሚወስን አካል ዉሳኔዉን እንዴት መወሰን እንዳለበት ወይም የዉሳኔዉ ዉጤት ምን መሆን እንዳለበት ምንም የሚለዉ ነገር የለም፥ ደግሞም የ”ራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን” መብት ለህዝብ የተሰጠ መብት መሆኑን ይናገራል እንጂ “ህዝብ” ማለት እንዲህ ማለት ነዉ ብሎ ትንታኔ ዉስጥ አይገባም። አንድ በግልጽ የሚናገዉ ነገር ግን አለ፥ እሱም የ”ራስን ጉዳይ በራስ መወሰን” ማለት ዉሳኔዉን የሚወስነዉ አካል ግለሰብ ይሁን ቤተሰብ ወይም ማህበረሰብ የራሱን ጉዳይ በተመለከተ ማንም ጣልቃ ሳይገባበት እራሱ ይወስናል ማለት ነዉ- ይህ ማለት ደግሞ የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚባለዉ መብት የአገራችን የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞች እንደሚነግሩን ለብሄሮች ብቻ የተሰጠ መብት አይደለም ማለት ነዉ። ግለሰቦችም የራሳቸዉን ጉዳይ በራሳቸዉ የመወሰን መብት አላቸዉ። ለምሳሌ አንድ
ግለሰብ የት መኖር እንደሚገባዉ፥ ምን አይነት ሃይማኖት መከተል እንደሚገባዉ፥ ምን አይነት ትምህርት መማር እንደሚገባዉ፥ ምን መስራትና የት መስራት እንደሚገባዉ፥ መሪዉ ማን መሆን እንደሚገባዉና በምርጫ ወቅት ማንን መምረጥ እንደሚገባዉ የሚወስነዉ እሱ እራሱ ነዉ ማለት ነዉ። ታዲያ ኢትዮጵያ ዉስጥ በዞን፥ በከተማዎችና በወረዳዎች ዉስጥ የሚኖረዉ ህዝብ ለምንድነዉ የራሱን ጉዳይ በራሱ እንዲወስን የማይፈቀድለት? መቼ ነዉ በከተማዎች የሚኖረዉ ህዝብ ልጆቹ በምን ቋንቋ መማር እንዳለባቸዉ እሱ እራሱ የሚወስነዉ? መቼ ነዉ በአዲስ አበባና በሌሎቹም የኢትዮጵያ ከተማዎች የሚኖረዉ ህዝብ ከንቲባዉንና የምክር ቤት አባላትን የሚመርጠዉ? ለምንድነዉ አዳማን፥ አዋሳንና ቢሾፍቱን በመሳሰሉ ህብረብሄር የአገራችን ከተማዎች ዉስጥ ያለዉ የፖሊስ ሃይል የሚያገለግለዉን ህዝብ የማይመስለዉ?

Comments
Post a Comment
Thank You!!