እራስን  በራስ  የማስተዳደር  መብትና  የኢትዮጵያ  ፌዴራሊዝም
ክፍል 3
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረዉ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለብሄር ብሄረሰቦች ከፍተኛ መብት ይሰጣል፥ ለምሳሌ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ አንድየኢትዮጵያ ብሄሮች፥ ብሄረሰቦች፥ ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸዉ ይላል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙዎቹ ክልሎች እስከነስያሜያቸዉ በአንድ ብሄር ዙሪያ የተገነቡ ስለሆነ በእነዚህ ክሎች ዉስጥ የሚኖር ከሌላ ክልል የመጣ ኢትዮጵያዊ እንደሁለተኛ ዜጋ ነው የሚታየዉ። ይህ ደሞ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ የፈጠረዉ ተራ ወሬ አይደለም። በከተማ ደረጃ ድሬደዋ፥ ሐረርና አዋሳ ዉስጥ የየአካባቢዉ ተወላጅ ባልሆኑ ዜጎች ላይ የሚደርሰዉን በደል መመልከት ይበቃል። በአካባቢ ደረጃ ደግሞ ከሶማሌ ክልል፥ ከጉጂ፥ ከጉራ ፈርዳና ከሌሎችም አካባቢዎች ቦታዉ የእናንተ አይደለምና ዉጡ ተብለዉ የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎችን መመልከቱ ይበቃል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የብሄር ፖለቲከኞች ስለኢትዮጵያ ፌዴራል ስርአት ሲያወሩ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ከዲሞክራሲ ጋር አለመተዋወቁ ነዉ እንጂ ሌላ ችግር የለበትም ይላሉ። ሌሎቻችንም ብንሆን ትኩረት ሰጥተን የምናወራዉ ስለዲሞክራሲና እሱን ተከትሎ ስለሚመጣዉ ምርጫ ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ በየክልሉ የሚታየው ትልቅ ችግር ግን የፍትና የእኩልነት አለመኖር እና የህግ የበላይነት አለመከበር ነዉ።  
ኢትዮጵያ ዉስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል፥ ግን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ስለተካሄደ ብቻ ኢትዮጵያ ዉስጥ መልካም የዲሞክራሲ ጅምር አለ ሊባል አይችልም። ለዚህ ዋና ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንደኛ- የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርአት የራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን መብት የሚሰጠዉ በክልል ደረጃ ብቻ ነዉ እንጂ በተለያያዩ የአስተዳደር እርከኖች ለሚኖረዉ ህዝብእራስን በራስ የማስተዳደርመብት አይሰጥም። ሁለተኛ- ኢትዮጵያ ዉስጥ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ የአጭርና የረጂም ግዜ ዉሳኔዎችን የሚወስኑ የክልል ፕሬዚደንቶች እና የከተማ ከንቲባዎች ተሿሚዎች ናቸዉ እንጂ በቀጥታ በህዝብ አይመረጡም። ስለዚህ እነዚህ ሁለት መዋቅራዊ ችግሮች ሳይፈቱ ምርጫ ስለተካሄደ ብቻ የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ስርአት ዲሞክራሲያዊ ነዉ ማለት አይቻልም። ዲሞክራሲ ለህብረተሰብ ያበረከተዉ ትልቁ ገጸበረከት የፖለቲካ ሥልጣንን ከፈላጭ ቆራጭ አምባገነኖች መዳፍ ዉስጥ አዉጥቶ የህዝብ ንብረት እንዲሆኑ ማድረጉ ነዉ። ፌዴራሊዝም ለህብረተሰብ ያበረከተዉ ትልቅ ስጦታ ደግሞ ህዝብ የፓለቲካ ሥልጣንን በሚኖርበት አካባቢና በማዕከል እኩል እንዲጋራዉ ማድረጉ ነዉ።

Comments

Popular Posts